ትንታኔ
ያ ትውልድ እና ዶ/ር ነገደ ጎበዜ
ባየ ተሻገር አስማማውኅዳር 5 ቀን 2019 ዓ.ም.

3,786 ቃላት · 57 ማስታወሻ
«የዛሬ ዓመት፣ አሥር ዓመት፣ ሀያ ዓመት .... የት እንደርስ ይሆን?»
መግቢያ
ሐምሌ 30 ቀን 1960 ዓ.ም. በጀርመን ሀገር በሐምቡርግ ከተማ አሥራ ሰባት ኢትዮጵያውያን በምሥጢር ተሰብስበው የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) ምሥረታን ባጠናቀቁበት ዕለት፣ የስብሰባውን ቃለ ጉባዔ የያዘው ኃይሌ ፊዳ በደብተሩ ላይ የሚከተለውን አስፍሮ ነበር፡- «በሐምቡርግ ከተማ፣ በጀርመን አገር በዚህ ቀን (6/8/68 እ.አ.አ.) አሥራ ሰባት ኢትዮጵያዊያን ተገናኝተን የሕይወታችንን ዓላማ ቀየስን። የዛሬ ዓመት፣ አሥር ዓመት፣ ሀያ ዓመት .... የት እንደርስ ይሆን?»1 ኃይሌ ፊዳ ያን ማስታወሻ ከጻፈ ከአሥራ አንድ ዓመት ገደማ በኋላ በደርግ እስር ቤት ውስጥ ያለ ፍርድ ተገድሏል።2 መኢሶን ዓላማው ሠምሮለት ሥልጣን ባይይዝም፣ ከኢሕአፓ ጋር ተጋርቶ በፕሮግራሙ ካሰፈራቸው ሐሳቦች የተወሰኑት፣ በኋላ ሥልጣን በያዙት ግንባሮች እጅ፣ የዛሬው ሕገ መንግሥት የማዕዘን ድንጋይ መሆናቸው አልቀረም።
ከዚያ ድርጅት መሥራቾች አንዱ የነበሩት ዶ/ር ነገደ ጎበዜ በኅዳር 2019 ዓ.ም. መጀመሪያ በሰማንያ ሦስት ዓመታቸው በስደት አርፈዋል።3 ዜናው ከተሰማ በኋላ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሐዘን መግለጫዎች እየተዘዋወሩ ይገኛሉ። እርሳቸውና ትውልዳቸው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ያሳደሩት ተጽዕኖ ቀላል ባለመሆኑ መታወሳቸው ተገቢ ነው። እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ከደጋጎቹ ጎን እንዲያሳርፍ፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸውም መጽናናትን እንዲሰጥ የእኔም ምኞት ነው።
በባህላችን «ሙት ወቃሽ አያድርገኝ» ይባላል፤ ያረፈን ሰው ድክመት መቆፈር ነውር መሆኑም እውነት ነው። ይህ ጽሑፍ ወቀሳ የለበትም አልልም፤ ወቀሳው ግን በባለታሪኩ ላይ ሳይሆን በአደባባይ በተደረጉ ምርጫዎች ላይ ነው። የሚመረምረውም የዶ/ር ነገደን የግል ሕይወት ሳይሆን፣ እርሳቸውና ድርጅታቸው ራሳቸው ያሳተሟቸውን ፕሮግራሞች፣ ቃለ ምልልሶችና ጽሑፎች፣ የትግል ጓዶቻቸው የጻፏቸውን መጻሕፍትና የታተሙ የታሪክ ጥናቶችን ነው። የሐዘን ጊዜ ለዚህ አይመችም የሚል ወገን ቅር ቢሰኝ እረዳለሁ። ለሀገር የታገለ ሰው የአደባባይ ሥራ ግን የሀገር ታሪክ አካል ነው፤ ታሪኩ በሙሉ ገጹ ሊታወስ የሚገባውም ሕይወቱ በሚዘከርበት በዚህ ሰዓት ነው።
የዚህ ጽሑፍ አቋም በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ የኢትዮጵያን የተማሪዎች ንቅናቄ የመራው የዶ/ር ነገደ ትውልድ፣ በተለምዶ «ያ ትውልድ» የሚባለው፣ ለዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ውድቀት መነሻ ነው የሚል ነው። መነሻ ስል የችግሩ መጀመሪያ ማለቴ አይደለም፤ ሀገሪቱ ዛሬ ወዳለችበት መንገድ የታጠፈችበትንና ዛሬ የምንኖርበት የፖለቲካ መዋቅር የተነደፈበትን ነጥብ ማለቴ ነው።
ይህን አቋም ከማስረዳቴ በፊት ግን ሦስት ነገሮችን መቀበል ተገቢ ነው። አንደኛው፣ ያ ትውልድ ለሀገሩና ለሕዝቡ ቅን ሐሳብ የነበረው መሆኑ ነው፤ የመኢሶኑ አንዳርጋቸው አሰግድ እንደጻፉት አብዛኞቹ ታጋዮች የተነሣሡት «የግል ጥቅምን በመሻት አልነበረም። ለወገናቸውና ለአገራቸው ባላቸው ፍቅር ነበር»፤4 ብዙዎቹም ለዚህ ዓላማ ሕይወታቸውን ሰጥተዋል። ሁለተኛው፣ ያ ትውልድ በትግል እፈታዋለሁ ብሎ የተረከበው ቀውስ እርሱ የፈጠረው አለመሆኑ ነው፤ የመሬት ይዞታ፣ የአስተዳደርና የእኩልነት ጥያቄዎች የተወለዱት፣ የአዱሊስ ወደብ ከተዘጋ በኋላ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውና የመንግሥትን ገቢ ከጉምሩክ ይልቅ ከገበሬው ጓዳ የሚሰበስበው ሥርዓት ለአንድ ሺሕ ሦስት መቶ ዓመት ገደማ በምድሪቱ ተንሰራፍቶ በመቆየቱ ነበር። ሦስተኛው፣ አንድ ትውልድ በጅምላ ሊፈረድበት አለመቻሉ ነው፤ ያ ትውልድ ብዙ ድርጅቶችን፣ ብዙ አቋሞችንና እጅግ ብዙ ሰለባዎችን የያዘ ነበር፤ ሁሉም በጅምላ ሊፈረጁ አይችሉም፤ ሊፈረጁም አይገባም። የዚህ ጽሑፍ ፍርድም በእያንዳንዱ ሰው ላይ ሳይሆን በትውልዱ መሪ ድርጅቶች ምርጫዎች ላይ ነው። እነዚህ ሦስቱም እውነት ናቸው።
ይሁን እንጂ ቅንነት ከተጠያቂነት ነጻ አያደርግም። ታሪክ አንድን ትውልድ የሚመዝነው በልቡ ሐሳብ ሳይሆን በምርጫዎቹና ምርጫዎቹ ባስከተሉት ውጤት ነው። የሕመሙ ሥር የቆየ ቢሆንም፣ የዚህ ጽሑፍ ክርክር ስለ ሕመሙ ሳይሆን ስለ ተመረጠው መድኃኒት ነው፤ ያ ትውልድ መነሻ የሚባለውም ለቆየ ሕመም የተሳሳተ መድኃኒት በመምረጡ ነው። በዚህ ሚዛን ሲመዘን፣ ኢትዮጵያ ዛሬ የባህር በር የሌላት፣ ፖለቲካዋ በብሔር የተዋቀረና ልዩነቷን በጠመንጃ የምትፈታ ሀገር የሆነችው ያ ትውልድ ያደረጋቸው ሦስት ምርጫዎች ወሳኝ ድርሻ ስለነበራቸው ነው ብሎ አቋም መያዝ ይቻላል። እነርሱም ለሌላ ሀገር የተሠራን የፖለቲካ ቀመር በኢትዮጵያ ልክ ሳያስተካክል መውሰዱ፣ የሀገርን አንድነት የትግል ስልት ማድረጉና ልዩነቱን በውይይት ሳይሆን በኃይል ለመፍታት መምረጡ ናቸው።
እነዚህን ምርጫዎች ለማየት የዶ/ር ነገደ ጎበዜ ሕይወት ጥሩ መስኮት ነው፤ እርሳቸው ከሌሎች የበለጠ ተጠያቂ ስለሆኑ ሳይሆን ሦስቱም ምርጫዎች በሕይወታቸው ውስጥ ተሰብስበው ስለሚገኙ ነው። ዶ/ር ነገደ ጎበዜ የአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር ፕሬዚደንት፣ የመኢሶን መሥራች፣ ደርግ ያቋቋመው የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት አባል፣ ለአምስት አሥርት ዓመታት ገደማ በስደት የኖሩ ተቃዋሚና በመጨረሻም የራሳቸው ትውልድ የሠራውን ሥርዓት አጥብቀው የተቹ ሰው ነበሩ። «ያ ትውልድ» የሚለው ስያሜም እዚህ የሚሠራበት በሰፊው ትርጉሙ ነው፤ ምክንያቱም አንዳርጋቸው አሰግድ ራሳቸው እንዳመለከቱት በ1983 ዓ.ም. በኢትዮጵያና በኤርትራ ሥልጣን የያዙት ግንባሮችም «እንደተቀሩት ሁሉ … በአብዛኛው ከተማሪው እንቅስቃሴ የመነጩ» የዚያው ትውልድ አካሎች ናቸው።5 ከ1966 ዓ.ም. ጀምሮ ለወታደራዊው መንግሥት ርዕዮት ያቀረቡት፣ የተቃወሙትና በ1983 ዓ.ም. ሥልጣን የያዙት ድርጅቶች በአብዛኛው ከአንድ የተማሪዎች ንቅናቄ የወጡ በመሆናቸው፣ ዋናው ተጠያቂነት ከዚያ ትውልድ ሊርቅ አይችልም። የ1955 ዓ.ም. የፌዴሬሽኑ መፍረስ፣ የቀዝቃዛው ጦርነትና የደርግ ወታደራዊ ምርጫዎች የየራሳቸው ድርሻ ነበራቸው፤ ለእነዚህ ሁሉ የፖለቲካ መልስ የሰጠው ግን ያ ትውልድ ነው።
1. የተውሶው ቀመር፣ ማርክሲዝም-ሌኒኒዝም፡- ከበርሊን ጉባዔ እስከ አንቀጽ 39
ቀመሩ እንዴት እንደተወሰደ ለመረዳት ከዶ/ር ነገደ የሕይወት ታሪክ መጀመር ይጠቅማል። ነገደ ጎበዜ ጥቅምት 4 ቀን 1936 ዓ.ም. በደሴ ከተማ የተወለዱ ሲሆን፣ አባታቸው አቶ ጎበዜ ጣፈጠ በሰሜን ኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስቴር ዳይሬክተር የነበሩና በ1943 ዓ.ም. ገደማ መሃይምነትን ለማጥፋት ያቀረቡት ጥናት በንጉሠ ነገሥቱ ተቀባይነት አግኝቶ የፕሮጀክቱ ኃላፊ የሆኑ የትምህርት ሰው ነበሩ። ነገደ ጎበዜ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደሴ ወይዘሮ ስኂን ትምህርት ቤት ከተከታተሉ በኋላ በአሥራ ሦስት ዓመታቸው አዲስ አበባ ጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት እንደገቡ፣ ከ1953 እስከ 1956 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተምረው በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዳገኙ ማኅደራቸው ያሳያል።6 በ1957 ዓ.ም. ገደማ ከፈረንሳይ መንግሥት ባገኙት ነጻ የትምህርት ዕድል ወደ ኤክስ-አን-ፕሮቫንስ ሄደው ሕግ ያጠኑ ሲሆን፣ በኅዳር/ታኅሣሥ 1967 ዓ.ም. «ፓርላማና ባህላዊ ማኅበረሰቦች በጥቁር አፍሪካ፡- የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥታዊ መንግሥትና የታንዛንያ ሪፐብሊክ ንጽጽራዊ ጥናት» በሚል ርዕስ የዶክትሬት ጥናታቸውን አቅርበው ተመርቀዋል።7
ይህ የሕይወት ታሪክ አንድ ነገር ያስረዳል። ነገደ ጎበዜ በዘመኑ ምርጥ ትምህርት ቤቶች የተማሩ የዚያ ትውልድ ተወካይ ከመሆናቸውም በላይ፣ በእነዚያው ዓመታት የሀገራቸውን ፓርላማና ባህላዊ ተቋማት ለዶክትሬት ያጠኑ ሰው ስለነበሩ፣ ያ ትውልድ የተሳሳተው ሀገሩን ባለማወቁ ነው ብሎ ማለፍ አይቻልም። ስሕተቱ የተፈጸመው ያን ዕውቀት ያስገባበትን የአስተሳሰብ ማዕቀፍ በመረጠበት ጊዜ ነው፤ ምርጫው የተደረገውም ነገደ ጎበዜ ከሐምሌ/ነሐሴ 1962 እስከ ሐምሌ/ነሐሴ 1963 ዓ.ም. በፕሬዚደንትነት በመሩት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር ውስጥ ነው።8
ምርጫው የተደረገበት ጥያቄ የብሔሮች ጥያቄ ነበር። በዘውዱ ሥርዓት ዘመን በብሔረሰቦች ላይ በደል ይደርስ እንደነበር ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ሲያስረዱ፣ ጭቆናው «የአስተዳደር ነፃነት ከማጣት አንስቶ፣ መሬት እስከ መነጠቅ» የዘለቀ እንደነበርና የብሔረሰቦቹ ባህልና ቋንቋም እንደተዋረደ ይገልጻሉ፤ በተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥም «በጥያቄው መፍትሔ ላይ የሐሳብ ልዩነት ቢፈጠርም፤ በጭቆናው ነባራዊነት ላይ ሙሉ ስምምነት ነበር» ይላሉ።9 በጭቆናው መኖር ላይ ስምምነት ስለነበረ፣ መመርመር የሚገባው ያ ትውልድ ለጥያቄው የመረጠው መልስ ነው።
በኅዳር 1962 ዓ.ም. ዋለልኝ መኮንን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ባቀረበው ጽሑፍ «ኢትዮጵያዊ ለመሆን የአማራን ጭምብል ማጥለቅ አለብህ» ካለ በኋላ «መገንጠል በራሱ ምንም ስሕተት የለበትም» የሚል አቋም አስፍሮ ነበር።10 የአውሮፓው የተማሪዎች ማኅበር ወደ ውሳኔ የደረሰው ያለ ጥናት አልነበረም፤ አንዳርጋቸው አሰግድ እንደሚገልጹት አባላቱ የኢትዮጵያን መንግሥት አመሠራረት፣ ማርክሲዝም ለብሔር ጥያቄ የሚሰጠውን መፍትሔ፣ የቅኝ ተገዢ ሀገሮችን ተሞክሮና ዓለም አቀፍ ሕግን «ለአንድ ዓመት ሙሉ» አጥንተዋል።11 ዋለልኝ ከጻፈ ሁለት ዓመት ሳይሞላ፣ በነሐሴ 1963 ዓ.ም. የአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር 11ኛ ጉባዔውን በበርሊን ሲያካሂድ የመገንጠልን መብት የሚቀበለው አቋም የንቅናቄው ይፋዊ መርሕ ሆነ። ፕሮፌሰር ባሕሩ ስለዚህ ጉባዔ ሲጽፉ፣ «የበርሊኑ ጉባዔ ውጤት ለአሥርት ዓመታት የኢትዮጵያ ግራ ክንፍ መለያ ሆኖ የቆየውንና በመጨረሻም በ1994ቱ [እ.አ.አ.፤ 1987 ዓ.ም.] የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ የሰፈረውን ቀመር መቀበል ነበር፤ ይኸውም "የብሔሮች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል" የሚለው ነው» ይላሉ።12 በጉባዔው ዋናው ክርክር የተካሄደው በእንድርያስ እሸቴና በብርሃነ መስቀል ረዳ መካከል ቢሆንም፣ አንዳርጋቸው አሰግድ እንደጻፉት በአብዛኛው ድምፅ የተላለፈው ውሳኔ «በወቅቱ የአኢተማ [የአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር] ፕሬዘዳንት በጉባዔው መክፈቻ ላይ ካደረገው ንግግር የተለየ አልነበረም»፤ የውሳኔው የመጀመሪያ ነጥብም የብሔሮች መብት «መገንጠልንም ጭምር የሚያጠቃልል ነው» ይላል፤ ሁለተኛውና ሦስተኛው ነጥቦች ደግሞ የብሔሮችን የትግል አንድነትና በፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድነትን ይጠይቃሉ።13 አንዳርጋቸው ፕሬዚደንቱን በስም አይጠቅሱም። የነገደ ጎበዜ ማኅደር የፕሬዚደንትነት ዘመናቸው እስከ ሐምሌ/ነሐሴ 1963 ዓ.ም. እንደነበር ስለሚገልጽ፣ ያ ፕሬዚደንት እርሳቸው ሳይሆኑ አይቀሩም፤ ይህ ግን የእኔ ድምዳሜ እንጂ የምንጩ ቃል አይደለም። የማኅበሩ መሪዎች በክርክሩ ስለነበራቸው ድርሻም የተሳታፊዎች ምስክርነት ይለያያል።14
ከአራት ዓመት በኋላም መኢሶን በ1967 ዓ.ም. መጨረሻ ወይም በ1968 ዓ.ም. መጀመሪያ ገደማ ባወጣው ፕሮግራሙ ቀመሩን ቃል በቃል ተቀብሎ፣ «የሁሉም ብሔረሰቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ድረስ ዕውቅና ያገኛል። የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች አንድነት በእኩልነት፣ በወንድማማችነትና በመከባበር አብረው ለመኖር ባላቸው ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ይሆናል» ሲል ደንግጓል፤15 አንዳርጋቸው አሰግድም ይህ አቋም «በመኢሶንና በኢሕአፓ ፕሮግራሞች ውስጥም የተካተተ» እንደነበር ያረጋግጣሉ።16 ያው ፕሮግራም የኢትዮጵያ ነጻነት፣ ሉዓላዊነትና አንድነት በጽናት እንደሚጠበቅም ይደነግጋል፤17 መኢሶን ዛሬ የአንድነት ኃይል ተደርጎ የሚታወሰውም ለዚህ ነው። የአንድነት ኃይል የሚባለው ድርጅት እንኳ የመገንጠልን መብት በፕሮግራሙ ማስፈሩ ግን፣ ቀመሩ በዚያ ትውልድ ላይ የነበረውን ኃይል ያሳያል።
«የሁሉም ብሔረሰቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ድረስ ዕውቅና ያገኛል።»
የራስን ዕድል በራስ መወሰን በተባበሩት መንግሥታት ቻርተርም የሰፈረ መርሕ መሆኑን፣ የብሔረሰቦች ንቅናቄዎችም ከተማሪዎቹ ቀድመው የነበሩ መሆናቸውን አንዳርጋቸው አሰግድ በትክክል ያስታውሳሉ፤18 ተገቢው መልስ ቋንቋንና ባህልን የሚያስከብር፣ ራስን በራስ ማስተዳደርንም በሕግ የሚያረጋግጥ ያልተማከለ አስተዳደር ነበር። ከሌኒንና ከስታሊን ጽሑፎች የተወሰደው ልዩ ነገር ሉዓላዊነትን ለብሔር መስጠቱና «እስከ መገንጠል» የሚለውን የመውጫ በር መክፈቱ ነው፤ የዚህ ጽሑፍ ትችትም በዚህ ላይ ብቻ ነው። አንዳርጋቸው አሰግድ ያ ትውልድ «ባዕድ ርዕዮተ ዓለምን ያመጣ» ተብሎ መወቀሱን አይቀበሉም፤ ርዕዮተ ዓለምና ቴክኖሎጂ ከጥንትም ጀምሮ ድንበር እየተሻገሩ የሚወራረሱ መሆናቸውን፣ ክርስትናና እስልምና፣ ፍትሐ ነገሥትና ዘመናዊ ትምህርትም ከውጭ የመጡ መሆናቸውን በማስታወስ፣ «ጃፓን እንደምን ሰለጠነች» እያሉ የጻፉትን የ1920ዎቹን ምሁራን እያመሰገኑ የ1960ዎቹን ታጋዮች በዚሁ መውቀስ ተገቢ አይደለም ይላሉ።19 ሐሳብ መዋስ በራሱ ስሕተት አለመሆኑ እውነት ነው፤ ይሁን እንጂ እርሳቸው ራሳቸው የጠቀሱት የጃፓን ምሳሌ መከራከሪያቸውን የሚያፈርስ ነው። ጃፓን ከምዕራቡ ዓለም ሳይንስንና ኢንዱስትሪን ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግሥትንና የሕግ ሥርዓትን ጭምር ወስዳለች፤ ከእኛ የምትለየው የተዋሰችውን በራሷ ልክ በማስተካከሏ ነው። ንጽጽሩ ተገቢ የሚሆነውም ጃፓንና ኢትዮጵያ በ1620ዎቹ በሮቻቸውን ለአውሮፓ ሚሲዮናውያን ዘግተው ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላ በ1840ዎቹ በመንግሥት ደረጃ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ግንኙነታቸውን ስላደሱ ነው፤ ከዚያ በኋላ ግን በጥቂት አሥርት ዓመታት ውስጥ ጃፓን ስትሠለጥን ኢትዮጵያ ወደ ኋላ ቀርታለች።20 ያ ትውልድ የተዋሰው የማርክሲዝም-ሌኒኒዝም ርዕዮት ግን ለኢትዮጵያ ባዕድ ከመሆኑም ባሻገር፣ ሀገሪቱ ምን እንደሆነች አስቀድሞ የሚበይንና መድኃኒቷንም አስቀድሞ የሚወስን የተጠናቀቀ ቀመር ነበር፤ ቀመሩ ኢትዮጵያን የብሔሮች እስር ቤት አድርጎ ስለሚተረጉም መፍትሔውንም «እስከ መገንጠል» ብሎ ይደመድማል። ማኅበሩ ለአንድ ዓመት ቢያጠናም፣ አንዳርጋቸው አሰግድ ራሳቸው እንደሚያምኑት የዘመኑ ተራማጆች «በአስተዳደር መዋቅር ዓይነት እና የመብቶቹን ሕጋዊ ይዘት እና አተገባበር በሚመለከቱ ጉዳዮች ረገድ ያቀረቧቸው ዝርዝሮች አልነበሩም»፤21 ቀመሩ በኢትዮጵያ ሕዝብ አሰፋፈርና ነባር ተቋማት ላይ ምን ውጤት ያመጣል የሚለው ጥያቄም መልስ ሳያገኝ ቀርቷል። ሶቪየት ኅብረትን ያፈረሳት ይህ ቀመር ነው ማለት አይደለም፤ ማዕከሉ በተዳከመበት በታኅሣሥ 1984 ዓ.ም. ግን ሀገሪቱ የተሰነጠቀችው ቀመሩ ባሰመራቸው የብሔር ሪፐብሊኮች ድንበር ነው። በኢትዮጵያ ያስከተለውን ውጤት ደግሞ ቀጥሎ እንመለከታለን።
ያ ትውልድ መርጦ የወሰደው የተውሶ ርዕዮት ፍሬ የታየው ከሃያ ዓመታት በኋላ ነው። በ1983 ዓ.ም. ሥልጣን የያዙት የብሔር ግንባሮች የበርሊኑን ቀመር የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ሲያደርጉት አዲስ ነገር አልፈጠሩም፤ አንዳርጋቸው አሰግድ እንደሚሉት አንቀጽ 39 «በመሠረቱ፣ የኢትዮጵያ ተራማጆችና ምሑራን በ60ዎቹ በድርጅት መርሆ ደረጃ ካስተጋቡትና መኢሶን እና ኢሕአፓ በየፕሮግራማቸው ካሠፈሩት የተለየ አልነበረም»፤ ሕገ መንግሥቱ አንቀጹን አካቶ መጽደቁም «እስከዛሬ የሚካሄደውን ውዝግብና ግጭት» አስከትሏል። አንዳርጋቸው ግን ጥፋቱን በአንቀጹ ላይ ሳይሆን ፌዴራላዊም ዴሞክራሲያዊም ባልሆነው አስተዳደር ላይ ያደርጋሉ።22 ይህ ግማሽ እውነት ነው፤ ሉዓላዊነትን ለብሔር የሰጠ መዋቅር ግን ዴሞክራሲ ቢኖርም እያንዳንዱን የፖለቲካ ልዩነት የማንነትና የድንበር ውዝግብ ያደርገዋል። ጆን ያንግ እንደመዘገበውም አንድ የሕወሓት ነባር ታጋይ የስታሊንን የ1905 ዓ.ም. (1913 እ.አ.አ.) «ማርክሲዝምና የብሔር ጥያቄ» ጽሑፍ የትግላቸው «መጽሐፍ ቅዱስ» እንደነበር የተናገረ ሲሆን፣ የሕገ መንግሥቱ የብሔር ትርጓሜም የስታሊንን ትርጓሜ በቅርበት የተከተለ ነው።23 ስለዚህ በሐምቡርግ የተሰበሰቡት የመኢሶን መሥራቾችና በደደቢት የተሰበሰቡት የሕወሓት መሥራቾች የፖለቲካ ተቀናቃኞች ቢሆኑም፣ ስለ ብሔሮች ጥያቄ የነበራቸው ቀመር በመርሑ ተመሳሳይ ነበር። ልዩነት አልነበረም ማለት አይደለም፤ አንዳርጋቸው አሰግድ እንደሚያስረዱት ኅብረ ብሔራዊ ድርጅቶቹ ዋናውን ቅራኔ በመደቦች መካከል ያዩ ሲሆን፣ የብሔር ድርጅቶቹ ግን በብሔረሰቦች መካከል አይተው አማራውን «ጨቋኝ ብሔር» ብለው ፈርጀዋል፤ ኅብረ ብሔራዊዎቹ መብቱን ከዲሞክራሲያዊ መብቶች እንደ አንዱ እንጂ እንደ ትግል ግብ አላዩትም፤ የኤርትራን ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ አድርጎ ማየትንም ተቃውመዋል። አንዳርጋቸው ራሳቸው ግን የሁለቱ ወገኖች አቋም «በአመዛኙ ተመሳሳይ» እንደነበር ይቀበላሉ።24 መርሑ ለብሔር ግንባሮቹ በር ከፍቷል፤ ሥራ ላይ ያዋሉትም የጠመንጃ ኃይል ያገኙት ግንባሮች ናቸው፤ ሻዕቢያ በኤርትራ መገንጠል፣ ሕወሓት በሕገ መንግሥቱ። መኢሶን እዚህ የተነሣው ቀመሩን ለእነርሱ ስላስተማረ ሳይሆን፣ የአንድነት ኃይል የሚባለው ድርጅት እንኳ ያንኑ ቀመር መያዙን ለማሳየት ነው።
ነገደ ጎበዜ በስደት ዘመናቸው ቀመሩ ያመጣውን ፍሬ አጥብቀው ተችተዋል። በ1987 ዓ.ም. አጋማሽ ስለ አዲሱ ሕገ መንግሥት ላዘጋጁት ጽሑፍ የሰጡት ርዕስ «ስለ ኢህአዴግ ህገ መንግሥት ስታሊናዊነትና አደገኛነት» የሚል ነበር፤25 በ2006 ዓ.ም. ባሳተሙት «ይድረስ ለግንቦት ከየካቲት» መጽሐፋቸው ደግሞ፣ ሕወሓት የሚመራው ገዥ ቡድን ለኤርትራ መገንጠል «ከሻዕቢያ ይበልጥ የተዋደቀ» መሆኑን አቶ ስብሐት ነጋ በይፋ መናገራቸውን አስታውሰው፣ ቡድኑን «"አስገንጣይ ተገንጣይ" ሊባል የሚችል ቡድን» ብለውታል።26 ትችታቸው ትክክል ነው፤ የኤርትራን መገንጠልም ከ1970 ዓ.ም. ጀምሮ ሲቃወሙ መኖራቸው መታወቅ አለበት። ሆኖም ሕገ መንግሥቱ ከስታሊን የወረሰው ዋናው ነገር፣ ማለትም «የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል» የሚለው የብሔሮች ቀመር፣27 በነሐሴ 1963 ዓ.ም. በበርሊን እርሳቸው በአመራር ውስጥ በነበሩበት ማኅበር ጉባዔ የጸደቀውና በኋላ በድርጅታቸው ፕሮግራም የሰፈረው ራሱ ነው። ዘር የዘራ ትውልድ አዝመራውን ሲተች፣ ማሳው እንዴት እንደታረሰ አብሮ ካልተናገረ ትችቱ ግማሽ ሆኖ ይቀራል። እኔ ባነበብኳቸው ሁለት ጽሑፎች፣ ማለትም በ1987 ዓ.ም. ጽሑፋቸውና በ2006 ዓ.ም. መጽሐፋቸው ላይ በወጣው ዳሰሳ፣ ትኩረታቸው በደርግና በኢሕአዴግ ላይ ነው፤ የበርሊኑ ውሳኔና የድርጅታቸው ፕሮግራም በውጤቱ ላይ የነበራቸውን ድርሻ አያነሡም። መጽሐፉን ራሱን ስላላነበብኩ፣ በዚያ ጽፈውት ከሆነ ለመታረም ዝግጁ ነኝ።
ቀመሩ በወረቀት ላይ ብቻ ቢቀር ኖሮ ጉዳቱ ባነሰ ነበር፤ ነገር ግን ያ ትውልድ ቀመሩን በወረቀት ላይ ከማስፈሩ በፊትም ሆነ በኋላ በአንድ ተጨባጭ ጥያቄ ላይ ሥራ ላይ አውሎታል፤ እርሱም የኤርትራ ጉዳይ ነው።
2. የሀገር አንድነት እንደ ትግል ስልት፡- የኤርትራ ጉዳይ
መኢሶን የመገንጠልን መብት በፕሮግራሙ ሲያሰፍር ዓላማው ሀገሪቱን መበተን አልነበረም። አንዳርጋቸው አሰግድ ፕሮፌሰር ባሕሩን ጠቅሰው እንደሚያስረዱት፣ የተማሪዎቹ ዓላማ ለኤርትራውያን የመገንጠል መብት ዕውቅና በመስጠት «ትግላቸውን የመላው ኢትዮጵያ ትግል አጋር ለማድረግ» እና ችግሩንም በዚያው ማዕቀፍ ውስጥ ለመፍታት ነበር።28 በወቅቱ በመኢሶን አባላት ይመራ የነበረው የማኅበሩ አመራርም፣ የብሔሮች መብት «የንጉሠ ነገሥቱን ሥርዓት የመገርሰሻ … መሣሪያ አይደለም» በማለት መብቱን እንደ መሣሪያ የማየትን አመለካከት ተቃውሞ እንደነበር ይገልጻሉ።29 ይህ ማብራሪያ ሊደመጥ ይገባል፤ ነገር ግን ድርጅቱ ራሱ በኋላ የሰጠው ቃል ከዚህ የተለየ ነገር ይናገራል። ነሐሴ 14 ቀን 1969 ዓ.ም. መኢሶን ከደርግ ጋር የነበረውን ትብብር ካቋረጠ በኋላ፣ ነገደ ጎበዜ የድርጅታቸው የውጭ ተወካይ ሆነው መስከረም 7 ቀን 1970 ዓ.ም. ለፈረንሳዩ «ሌ ሞንድ» ጋዜጣ ቃለ ምልልስ ሰጥተዋል።30 በኤርትራ ጉዳይ ሲጠየቁ፣ የድርጅታቸው ፕሮግራም የብሔረሰቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት «እስከ መገንጠል መብት ድረስ» እንደሚቀበል፣ የኤርትራ ችግርም በጦር ኃይል ሳይሆን በሰላማዊ ድርድር መፈታት እንዳለበት፣ ይህ ማለት ግን ድርጅታቸው በወቅቱ ሁኔታ የኤርትራን መገንጠል ያራምዳል ማለት እንዳልሆነ ከገለጹ በኋላ የሚከተለውን ተናግረዋል፡- «በቀድሞው ሥርዓት ዘመን አድሓሪ ኃይሎች ሁሉ የኤርትራን መገንጠል ይቃወሙ ነበር፤ እኛ ግን ያ ትግል የኃይለ ሥላሴን ሥርዓት ስላዳከመና በዚህም የአብዮተኛውን ወገን ስላጠናከረ ደግፈነዋል። በዓለም ዙሪያ የነበሩ ተራማጅ ኃይሎች አቋምም ይኸው ነበር። ዛሬ ሁኔታዎች ተለውጠዋል። የቀድሞው አልጋ ወራሽ እንኳ የኤርትራን ነጻነት ይደግፋሉ። … የዓረብ አድሓሪ መንግሥታት ለኤርትራ ግንባሮች የሚሰጡት ርዳታም ለውጡ በዓለም አቀፍ ደረጃ መካሄዱን ያሳያል። በእንዲህ ያለ ሁኔታ ድርጅታችን ዛሬ የኤርትራን መገንጠል ይቃወማል።»31
«ያ ትግል የኃይለ ሥላሴን ሥርዓት ስላዳከመና በዚህም የአብዮተኛውን ወገን ስላጠናከረ ደግፈነዋል።»
ይህ መልስ ያለ መሸፋፈን የተሰጠ በመሆኑ የዚያን ትውልድ አስተሳሰብ ከማንኛውም ትንታኔ በተሻለ ያሳያል። የኤርትራ ግንባሮች ትግል የተደገፈው ለኤርትራ ሕዝብ መብት ሲባል ብቻ ሳይሆን የአጼውን ሥርዓት ስለሚያዳክምም ነው፤ ሥርዓቱ ከወደቀ በኋላ ደግሞ፣ የኃይሎች አሰላለፍ ተለውጧል በሚል ምክንያት፣ አቋሙ ተለውጧል። በዚሁ መልስ «በአሁኑ ጊዜ የአብዮቱ ጉዳይ ከሀገራችን የግዛት አንድነት ጥያቄ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው» ማለታቸውም፣32 በሁለቱም ጊዜ መመዘኛው የሀገር አንድነት ሳይሆን የአብዮቱ ጥቅም እንደነበር ያሳያል። ይህ በሌኒናዊው አስተምህሮ ወጥ አቋም ነው ሊባል ይችላል። ችግሩም እዚያው ላይ ነው፡- አስተምህሮው የሀገርን አንድነት ሥልጣን ላይ ባለው ኃይል ማንነት ላይ የተንጠለጠለ ያደርገዋል። የዚህ ጽሑፍ ቀይ መስመር እዚህ ነው፡- መንግሥት ቢሳሳት ይታረማል፤ የተሰጠ ግዛትና የባህር በር ግን አይመለስም፤ ስለዚህ የሀገር አንድነት ከሥርዓት ጋር በአንድ ሚዛን መደራደሪያ አይሆንም። ያ ትውልድ ይህን መስመር ተሻግሯል። በሌላ አነጋገር፣ የሀገሪቱ ግዛታዊ አንድነት ለዚያ ትውልድ በራሱ የሚጠበቅ መርሕ ሳይሆን፣ እንደ ሁኔታው የሚከፈትና የሚዘጋ የትግል ስልት ነበር። ነገደ ጎበዜ ራሳቸው እንዳሉት ይህ የመኢሶን ብቻ ሳይሆን በዘመኑ የነበሩ ተራማጅ ኃይሎች የጋራ አቋም ስለነበር፣ ኃላፊነቱም የጋራ ነው። የትውልዱ ስሕተት የመገንጠልን በር እንደ ስልት ከፍቼ እንደ ስልት እዘጋዋለሁ ብሎ ማሰቡ ነው። አጼውን ለማዳከም የተደገፈው ትግል አጼው ከወደቁ በኋላ አልቆመም። ተማሪዎቹ ኤርትራን አላስገነጠሉም፤ ጦርነቱን በ1983 ዓ.ም. ያሸነፈው ሻዕቢያ ነው። የእነርሱ ድርሻ መገንጠልን መርሕ አድርገው ማስተማራቸው ነው። ኅብረ ብሔራዊ ድርጅቶቹ የኤርትራን ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ አድርጎ ማየትን ቢቃወሙም፣ የከፈቱት በር በእነርሱ ቁጥጥር ሥር አልቀረም፤ ከዚያው ንቅናቄ የወጣው ሕወሓት፣ አቶ ስብሐት ነጋ እንዳሉት፣ ለኤርትራ መገንጠል «ከሻዕቢያ ይበልጥ» ታግሏል። በ1983 ዓ.ም. ሥልጣን የያዘው መንግሥትም በ1985 ዓ.ም. የኤርትራን ነጻነት ያለ ቅድመ ሁኔታ፣ የሉዓላዊ የባህር በር ጥያቄን ሳያነሣ ተቀብሏል፤33 ኢትዮጵያም የባህር በሯን አጥታለች። አንድን መንግሥት ለመጣል ሲባል የሀገርን ዘላቂ ጥቅም መደራደሪያ ያደረገ ትውልድ፣ ዓላማው ምንም ያህል ቅን ቢሆን፣ ለውጤቱ ከተጠያቂነት አያመልጥም።
ግብን ለማሳካት ሲባል ከማንኛውም ኃይል ጋር መሰለፍን የሚፈቅደው ይህ አስተሳሰብ በኤርትራ ጉዳይ ብቻ አልተወሰነም፤ መኢሶን ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ ለወታደራዊው መንግሥት የሰጠው ሂሳዊ ድጋፍና ከ1968 ዓ.ም. ጀምሮ የገባበት ቀጥተኛ ትብብርም የዚሁ አስተሳሰብ ቅጥያ ነው።
3. ልዩነትን በኃይል መፍታት፡- ከወታደራዊው መንግሥት ጋር የተደረገው ትብብርና መጨረሻው
ነገደ ጎበዜ በየካቲት 1967 ዓ.ም. ገደማ ወደ ኢትዮጵያ በተመለሱበት ወቅት መኢሶን፣ የገጠር መሬት አዋጅ መታወጁን ምክንያት በማድረግ፣ «ሂሳዊ ድጋፍ/ገንቢ ተቃውሞ» የተባለውን የትግል ስልት ቀይሶ ነበር።34 ስልቱ በወቅቱ ምክንያት ነበረው፤ የመሬት ላራሹ አዋጅ ተማሪዎቹ ለአሥር ዓመታት የጮኹለትን ጥያቄ የመለሰና የገባር ሥርዓትን ያፈረሰ፣ እስከ ዛሬም የዚያ ትውልድ ዋና ስኬት ሆኖ የሚቆጠር እርምጃ ነው። ይሁን እንጂ መኢሶን አዋጁን በመደገፍ አላቆመም፤ ወታደራዊው መንግሥት የሚቆጣጠረውን ኃይል ለራሱ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ ለማድረግ በማሰብ ወደ መንግሥት መዋቅር ገባ። በኅዳር/ታኅሣሥ 1968 ዓ.ም. ደርግ «የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት»ን እንዲያቋቁሙ ከጠየቃቸው አሥራ አምስት ምሁራን አምስቱ የመኢሶን አባላት የነበሩ ሲሆን፣ ነገደ ጎበዜ ከእነርሱ አንዱ ነበሩ።35 በጽሕፈት ቤቱ ውስጥ የማስታወቂያና የፖለቲካ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ የየካቲት 66 የፖለቲካ ትምህርት ቤት አቋቋሚዎች አንዱና የ«አብዮታዊት ኢትዮጵያ» መጽሔት አዘጋጅ ሆነው እስከ ነሐሴ 1969 ዓ.ም. ያገለገሉ ሲሆን፣36 ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የጦር መሣሪያ ለመጠየቅ ወደ ቻይና የመራው ቡድን አባልም ነበሩ።37 ሃሊዴይና ሞሊኑ እንደጻፉት በታኅሣሥ 1969 ዓ.ም. ገደማ የጽሕፈት ቤቱ ማዕከላዊ ምክር ቤት በመኢሶን አባላት የተያዘ ነበር፤ ድርጅቱም በዚህ አማካይነት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ በቀበሌዎችና በሠራተኛ ማኅበራት ውስጥ ሰፊ ተጽዕኖ ገንብቷል።38
ምሁሩ ለወታደሩ ርዕዮት፣ ፕሮግራምና ካድሬ ሲያቀርብ ወታደሩ ለምሁሩ ቢሮና ጥበቃ አቀረበ፤ እያንዳንዱ ሌላውን እየተጠቀመበት እንደሆነ ያስብ ነበር። ትብብሩ ግን መኢሶንን ከደርግ የኃይል እርምጃዎች ጋር አስተሳስሮታል። ሃሊዴይና ሞሊኑ መኢሶን በቀድሞ ተቀናቃኙ በኢሕአፓ ላይ የተወሰደውን የሽብር እርምጃ አጥብቆ ደግፏል ሲሉ የጻፉ ሲሆን፣ በዚያው ዓረፍተ ነገር የመኢሶን መሪዎች በኢሕአፓ መገደላቸውንም ይጠቅሳሉ።39 አንዳርጋቸው አሰግድም፣ ከመስከረም 1969 ዓ.ም. ጀምሮ የመኢሶን አባሎች በኢሕአፓ የታጠቁ ቡድኖች ይገደሉ እንደነበር ካስታወሱ በኋላ፣ መኢሶን በመጋቢት 1969 ዓ.ም. በተካሄደው የትጥቅ ማስፈታት አሰሳ ውስጥ መሳተፉን ይገልጻሉ። በዚያ አሰሳ ወቅትና በሜይ ዴይ ዋዜማ (ሚያዝያ 22 ቀን 1969 ዓ.ም.) በተፈጸሙት ግድያዎች ላይ አመራሩ መግለጫ ሳይሰጥ መቅረቱም «ስሕተት» እንደነበር ያምናሉ።40 መኢሶን ከደርግ ከተለየ በኋላም በዚያ ዘመን ስለነበረው ድርሻ ራሱን ወዲያው አልመረመረም። ከላይ በተጠቀሰው የ«ሌ ሞንድ» ቃለ ምልልስ፣ ድርጅቱ ከደርግ ጋር በነበረበት ዘመን ስለተፈጸሙት ግድያዎች ሲጠየቅ፣ ሀገሪቱ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እንደነበረችና ግድያ በሁለቱም ወገን እንደተፈጸመ ካስረዳ በኋላ፣ ስለ ግድያው የሚወጡት ዘገባዎች የዓለምን አስተያየት ለማሳሳት ሆን ተብሎ የተጋነኑ ናቸው የሚል መልስ ሰጥቷል፤ ሃሊዴይና ሞሊኑም ድርጅቱ በዚያ ወቅት ራሱን ከመውቀስ ይልቅ ድርሻውን ትክክል አድርጎ ለማቅረብ መሞከሩን ጽፈዋል።41 ከመለያየቱ በኋላ የቀጠለውን ቀይ ሽብር ነገደ ጎበዜ በ1972 ዓ.ም. ገደማ ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ «መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማሸበር የተደራጀ» ብለውታል፤ በዚያው ቃለ ምልልስ የራሳቸው ድርጅት አባል ያልሆኑ እስረኞችም እንዲፈቱ መጠየቃቸውን፣ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሁሉ የሚሳተፉበት ግንባር እንዲመሠረትም ጥሪ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።42
የትብብሩ መጨረሻ የመጣው በፍጥነት ነው። በሐምሌ 1969 ዓ.ም. ደርግ በጽሕፈት ቤቱ ላይ የነበረውን ቁጥጥር ዳግም አጽንቶ የፖለቲካ ትምህርት ቤቱንም በራሱ ቋሚ ኮሚቴ ሥር ካደረገ በኋላ፣43 መኢሶን ነሐሴ 14 ቀን 1969 ዓ.ም. ከሚያዝያ 1968 ዓ.ም. የጀመረውን «የአሥራ ሰባት ወራት ትብብሩን» አቋርጦ ወደ ኅቡዕ ገባ፤44 ውጤቱንም አንዳርጋቸው አሰግድ «በርካታ ከፍተኛ አመራሮቹ፣ ዓባላቱና ወዳጆቹ በጥቂት ቀናት ውስጥ ተገደሉ። ታፈሱ። ለበርካታ ዓመታት እሥር ተዳረጉ። ሌሎችም ተሰደዱ» ሲሉ ይገልጹታል።45 በሐምቡርግ «የት እንደርስ ይሆን?» ብሎ የጻፈው ኃይሌ ፊዳ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ተይዞ ከሁለት ዓመት ገደማ እስር በኋላ ያለ ፍርድ ተገድሏል።46 ነገደ ጎበዜ በዚያ ወቅት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር ጉባዔ ላይ ለመገኘት ሎዛን ስለነበሩ በድርጅታቸው መመሪያ በዚያው ቀሩ።47 የጦር ኃይል ላለው ወገን ሐሳብና ካድሬ ማቅረብ በኃይሉ ላይ ሥልጣን እንደማያስገኝ መኢሶን የተማረው በዚህ መንገድ ነው፤ ፕሮግራሙን ለማስፈጸም በወታደር ጠመንጃ ጥላ ሥር የሠራው ድርጅት፣ የራሱ የጸጥታ ክፍል እንኳ ሳይኖረው፣ ከኢሕአፓ ጥይትም ከደርግ ጥይትም አላመለጠም።
ከዚያ በኋላ የተደረገው ሙከራም የዚያን ዘመን ፖለቲካ ሌላ ባሕርይ ያሳያል። ከመስከረም እስከ ሚያዝያ 1970 ዓ.ም. ነገደ ጎበዜ በኩባና በየመን መሪዎች ተጋብዘው በሁለቱ ሀገሮች የቆዩ ሲሆን፣ የራሳቸው ማኅደር እንደሚገልጸው የሁለቱ ሀገሮች መሪዎች በኮሎኔል መንግሥቱና በመኢሶን መካከል ውይይት ለማዘጋጀት ጥረት በማድረጋቸው ነገደ ጎበዜ ወደ አዲስ አበባ ሄደው በኩባ ኤምባሲ ውስጥ ተቀምጠዋል፤48 የጀርመኑ «ዲ ቬልት» ጋዜጣ በወቅቱ እንደዘገበው፣ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት፣ ኮሎኔል መንግሥቱ ሃቫናን በጎበኘበት ሳምንት፣ ከፓሪስ በኤደን በኩል በምሥጢር ነበር።49 ሙከራው ዕርቅን ለማምጣት የታሰበ በመሆኑ በራሱ አይወቀስም፤ ውይይቱ ግን ሳይጀመር ቀርቷል። ይሁንና የኢትዮጵያ መንግሥትና አንድ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅት ለመነጋገር የሃቫናና የኤደን አደራዳሪነት ያስፈለጋቸው መሆኑ፣ ውይይት ለማስጀመር የተደረገው ሙከራም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በውጭ ሀገር ኤምባሲ ግቢ ተወስኖ መቅረቱ፣ ያ ትውልድ የሀገሩን ጉዳይ ራሱ መፍታት ወደማይችልበት ደረጃ መድረሱን ያሳያሉ። ደርግ በሶቪየት ኅብረትና በኩባ፣ የኤርትራ ግንባሮች በዓረብ መንግሥታት፣ ሌሎቹ ድርጅቶችም በየጎረቤት ሀገሩ ድጋፍ ላይ ተመርኩዘው ስለነበር፣ የሀገሪቱ ጉዳዮች የሚወሰኑበት ቦታ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይበልጥ ከሀገር ውጭ ሆነ፤ ዛሬም የኢትዮጵያ ጦርነቶችና ድርድሮች በውጭ ዋና ከተሞች መወሰናቸው የዚሁ ልማድ ቅጥያ ነው።
የዚህን ምዕራፍ ፍርድ ከማንም በላይ ግልጽ አድርገው ያስቀመጡት የዚያ ትውልድ አባላት ራሳቸው ናቸው። አንዳርጋቸው አሰግድ በዘመኑ የነበሩት ድርጅቶች «በጥሞና ለመነጋገርና ለመደማመጥ ያልቻሉ»፣ «ባለመስማማታቸው ተስማምተው በሠላምና በመከባበር ለመለያየት የቻሉ» እንዳልነበሩ ከመሰከሩ በኋላ፣ የፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀን ሐሳብ በራሳቸው ትርጉም ጠቅሰው፣ መኢሶንና ኢሕአፓ «ለመወያየትና ትብብርን ለመገንባት በይበልጥ ክፍት ቢሆኑ ኖሮ፤ ልዩነቶቻቸው የማይፈቱ አልነበሩም። … ትውልዱም ይተርፍ ነበር» የሚለውን «እጅጉን ዕውነት ነው» ብለው ይቀበላሉ፤50 «የአብዮቱ ዘመን ታጋዮች መሠረታዊ ስህተት በእውነትም ለመወያየት አለመፈለጋቸው፣ የሌላውን ሃሳብ አለማክበርና ትብብርን ለመገንባት አለመቻላቸው ነው» ሲሉም ይደመድማሉ።51 ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴም በተማሪዎች ንቅናቄ ታሪካቸው የንቅናቄው ሁለት ዋና ቅርሶች መቻቻል የሌለበት የፖለቲካ ባህልና የብሔሮች ጥያቄ አቀራረብ በፖለቲካው ላይ ያሳደረው ዘላቂ ተጽዕኖ መሆናቸውን፣ ሁለቱም አሉታዊ መሆናቸውንም አስረድተዋል።52 ልዩነትን በኃይል መፍታት ከዚያ ትውልድ በፊትም የነበረ ነው፤ ያ ትውልድ ግን ልማዱን በርዕዮትና በድርጅት አስታጥቆ አውርሶናል። ዛሬ በትግራይ፣ በአማራና በኦሮሚያ የሚካሄዱት ጦርነቶችም ከዚህ ውርስ ተነጥለው ሊታዩ አይችሉም፤ ይህ ግን ዛሬ ጦርነቱን የሚመራውን መንግሥትም ሆነ በጦርነቱ የተሰለፍነውን ወገኖች ሁሉ ከተጠያቂነት ነጻ አያደርግም።
«ለመወያየትና ትብብርን ለመገንባት በይበልጥ ክፍት ቢሆኑ ኖሮ፤ ልዩነቶቻቸው የማይፈቱ አልነበሩም። … ትውልዱም ይተርፍ ነበር።»
ነገደ ጎበዜ በኋለኛው ዘመናቸው ከዚህ የተለየ መንገድ መከተላቸው ለእርሳቸው ክብር መነገር አለበት። በ1972 ዓ.ም. ገደማ በፈረንሳይ ለኢትዮጵያ የሚሠራ የአጋርነት ኮሚቴ አቋቁመዋል፤ በ1982 ዓ.ም. ገደማ በፓሪስ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም የሚሠራ የጥናትና የተግባር ቡድን አቋቁመው፣ በሰኔ/ሐምሌ 1985 ዓ.ም. «ከጦርነት ወደ ሰላም፣ ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ» በሚል ርዕስ በፓሪስ ጉባዔ አዘጋጅተዋል፤ በኅዳር/ታኅሣሥ 1986 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተዘጋጀውን የሰላምና የዕርቅ ጉባዔ በሊቀ መንበርነት መርተዋል፤ በ1990 ዓ.ም. ገደማ ደግሞ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ እንዲኖራቸው የተጠራውን ጉባዔ አስተባብረው የተቃዋሚ ድርጅቶችን ኅብረት በሊቀ መንበርነት መርተዋል። ከ1989 ዓ.ም. ገደማ ጀምሮም ሁለት የሬዲዮ ፕሮግራሞችን መሥርተው አገልግለዋል።53 በመስከረም 1970 ዓ.ም. ቃለ ምልልሳቸው ከኢዲዩና ከኢሕአፓ ጋር ኅብረት መፍጠር «የማይታሰብ» ነው ብለው የነበረ ቢሆንም፣54 ከ1972 ዓ.ም. ገደማ ጀምሮ በስደት ዘመናቸው ሁሉ ትብብርንና ውይይትን ሲፈልጉ ኖረዋል፤ ትምህርቱ ግን የደረሰው ብዙ ጓዶቻቸው ካለቁ በኋላ ነው፤ ለመነጋገር ፈቃደኛ በሆኑበት ጊዜ ሥልጣኑ ለመነጋገር ፈቃደኛ ባልሆነው የዚያው ትውልድ ሌላ ክንፍ እጅ ገብቶ ነበር። በ2006 ዓ.ም. መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ «ዛሬም ከመቶ ዓመታት በኋላ እነዚህኑ ጥያቄዎች አንግበን ለመዋደቅ የተገደድንበት ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን» ሲሉ የጻፉት ዓረፍተ ነገር የዚያ ትውልድ ውድቀት ምስክር ቢሆንም፣ ጥያቄዎቹ ሳይመለሱ የቀሩበትን ምክንያት ሲያስረዱ ትኩረታቸው አብዮቱን በቀለበሱት በደርግና በኢሕአዴግ ላይ ነው።55 እንደ አንዳርጋቸው አሰግድ ራሱን የመረመረ ቢኖርም፣ ይህ ምርመራ የደረሰው ዘግይቶና ከጥቂቶች ነው። ሌሎችን መተቸትና ራስን መመርመር የተለያዩ ነገሮች ናቸው፤ ያ ትውልድ ለሃምሳ ዓመታት በመጀመሪያው ሲበረታ በሁለተኛው ግን ደክሟል።
ማጠቃለያ
ኃይሌ ፊዳ በሐምቡርግ «የዛሬ ዓመት፣ አሥር ዓመት፣ ሀያ ዓመት .... የት እንደርስ ይሆን?» ብሎ ከጻፈ ሃምሳ ስምንት ዓመታት አልፈዋል፤ መልሱንም ዛሬ እናውቀዋለን። ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ድርጅቱ ተበትኖ ቃለ ጉባዔ ያዡ ታሰረ፤ ከሃያ አምስት ዓመት በኋላ ኤርትራ ነጻ ሀገር ሆና ኢትዮጵያ የባህር በሯን አጣች፤ ከሃያ ሰባት ዓመት በኋላ «እስከ መገንጠል» የሕገ መንግሥት አንቀጽ ሆነ፤ ከሃምሳ ስምንት ዓመት በኋላ ደግሞ፣ ከመሥራቾቹ አንዱ በስደት ባረፉበት በዚህ ዓመት፣ ሀገሪቱ በብሔር መስመር በተከፈሉ ጦርነቶች ውስጥ ትገኛለች። ያ ትውልድ ያለመው የዜጎች መብት የተረጋገጠባትን፣ ረሀብና ችጋር «የትላንት የሆኑባትን»፣ የሕዝቦቿ አንድነት የጸናባትንና በዓለም መድረክ የታፈረችና የተከበረችን ኢትዮጵያ ነበር፤56 የተገኘው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። ስለዚህ ያ ትውልድ ለዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ውድቀት መነሻ ነው ሲባል ሀገሩን ስለጠላ ወይም ክፉ ስለነበረ አይደለም፤ ሀገሩን እየወደደ ለሌላ ሀገር የተሠራን ቀመር በኢትዮጵያ ልክ ሳያስተካክል ስለወሰደ፣ የሀገርን አንድነት የትግል ስልት ስላደረገና ልዩነቱን በውይይት ሳይሆን በኃይል ለመፍታት ስለመረጠ ነው፤ ከእነዚህ ምርጫዎችም ሁለት ነገሮች ተከትለዋል፡- የውጭ ጥገኝነትና ራስን በጊዜው አለመመርመር። ዶ/ር ነገደ ጎበዜ በእነዚህ ምርጫዎች ሁሉ ውስጥ የነበሩና በኋለኛው ዘመናቸው ውጤቱን ከተቹት ሰዎች አንዱ በመሆናቸው፣ ሕይወታቸው የዚያ ትውልድ ታሪክ ማጠቃለያ ነው ማለት ይቻላል።
ከዚህ ታሪክ የሚገኘው ትምህርት ለዛሬው ትውልድ ነው፤ ምክንያቱም ያ ትውልድ ከመድረኩ እየተሰናበተ ቢሆንም የሠራው ቤት አሁንም ቆሞ እኛ የምንኖረው በውስጡ ነው። የውጭ ሐሳብ ሁሉ «ለማን ተሠራ? በእኛ ሁኔታ ምን ውጤት ያመጣል?» ተብሎ ሳይመዘን መወሰድ የለበትም። አንድን መንግሥት መቃወም የሀገርን ግዛት፣ ሉዓላዊነትና የባህር በርን መደራደሪያ ለማድረግ ምክንያት ሊሆን አይገባም። ልዩነትም በጠመንጃ ሳይሆን በውይይት መፈታት አለበት፤ አንዳርጋቸው አሰግድ ለዛሬዎቹ ባለሥልጣናትና ታጋዮች እንደመከሩት «ባለመስማማታቸው ተስማምተው በሰላምና በመከባበር ለመለያየት የመቻልን ጥበብ የራሳቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል።»57 ይህ ምክር ለሌሎች ብቻ የተሰጠ አይደለም። ዛሬ በብሔር ተደራጅተን የምንታገል ኃይሎች ሁሉ፣ እኔ ራሴ የተሳተፍኩበትን የአማራ ብሔርተኝነት ጨምሮ፣ በዚያ ትውልድ መዝገበ ቃላት የምንናገር፣ ልዩነትን በጠመንጃ ወደ መፍታት የተሻገርንና ድጋፍን ከውጭ እስከ መፈለግ የሚደርሱ ወገኖች ያሉብን በመሆናችን፣ ያን ትውልድ እየወቀስን ምርጫዎቹን መድገማችንን መቀበል አለብን። ራስን ከጥቃት መከላከልና የፖለቲካ ልዩነትን በጠመንጃ መፍታት አንድ አይደሉም፤ የመጀመሪያው ወደ ሁለተኛው እንዳይሻገር መጠበቅ ግን የእኛ ዕዳ ነው።
«ባለመስማማታቸው ተስማምተው በሰላምና በመከባበር ለመለያየት የመቻልን ጥበብ የራሳቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል።»
ፈጣሪ የዶ/ር ነገደ ጎበዜን ነፍስ በአጸደ ገነት ያኑርልን፤ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸውም መጽናናትን ይስጥልን። ለእርሳቸውና ለትውልዳቸው ልንሰጠው የምንችለው ተገቢ ክብር ታሪካቸውን ያለ ሽንገላና ያለ ጥላቻ መመርመርና ከምርጫዎቻቸው መማር ነው፤ ይህን ካላደረግን የሐምቡርጉ ጥያቄ ለእኛ ትውልድም ተመሳሳይ መልስ ይኖረዋል።
ስለ ዘመን አቆጣጠር፡- በዚህ ጽሑፍ የተጠቀሱት ዘመናት በሙሉ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ናቸው። ምንጩ ወሩን ብቻ በአውሮፓውያን አቆጣጠር በሰጠባቸው ቦታዎች ሁለቱ ተጓዳኝ የኢትዮጵያ ወራት በሕዝባር (ለምሳሌ ኅዳር/ታኅሣሥ) ተጽፈዋል (ትክክለኛው ቀን ወይም ወር ከኢትዮጵያ ምንጭ በሚታወቅበት ቦታ ግን እርሱ ተሰጥቷል)፤ ዓመቱን ብቻ በሰጠባቸው ቦታዎች ደግሞ ልወጣው ግምታዊ በመሆኑ «ገደማ» ተብሎ ተመልክቷል። በቀጥታ ጥቅሶች ውስጥ ያሉና በግርጌ ማስታወሻዎች የተጠቀሱ የውጭ ምንጮች ዘመናት ግን እንደ ምንጮቹ በአውሮፓውያን አቆጣጠር (እ.አ.አ.) ተትተዋል፤ በአንዳንድ ቦታ ሁለቱም አቆጣጠሮች አብረው ተሰጥተዋል፤ በጥቅስ ውስጥ በአራት ማዕዘን ቅንፍ [ ] ያለው የጸሐፊው ነው።
ማስታወሻዎች
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፡ አንዳንድ ማስታወሻዎች (የካቲት 2016 ዓ.ም.)፣ ገጽ 24። ጸሐፊው የመኢሶን አባል የነበሩ ሲሆን፣ መሥራች አባላቱ 25፣ በጉባዔው የተገኙት 17 እንደነበሩ ይገልጻሉ። ጽሑፉ በ https://amharic.borkena.com ላይ ይገኛል። ቃለ ጉባዔው የተጻፈበት ቀን 6/8/68 እ.አ.አ. (ኦገስት 6 ቀን 1968) በኢትዮጵያ አቆጣጠር ሐምሌ 30 ቀን 1960 ነው፤ ጸሐፊው በገጽ 24 የድርጅቱን ምሥረታ ሐምሌ 26 ቀን 1960 ዓ.ም. ብለው ይጠቅሳሉ። ↩
- Andargachew Tiruneh, «The Ethiopian Revolution (1974 to 1984)» (PhD thesis, London School of Economics, 1990), p. 326: «arrested with several of his close associates some 40 kilometres to the north of Addis Ababa, tortured and summarily executed while in prison some two years later». ↩
- «Dr. Negede Gobeze, Veteran Ethiopian Leftist Leader and MEISONE Founder, Passes Away at 83», Fidel Post, 13 November 2026, https://fidelpost.com. ዜናው ኅዳር 4 ቀን 2019 ዓ.ም. የተዘገበ ሲሆን፣ ዘገባው ያረፉበትን ቀንና ቦታ አይገልጽም፤ የትውልድ ዘመናቸውን 1950 እ.አ.አ. ማለቱም ከሰጠው ዕድሜና ከራሳቸው ማኅደር (1943 እ.አ.አ.) ጋር አይጣጣምም። መሥራችነታቸውን በተመለከተ፡- «Biography», Negede Gobezie Archives, https://www.negedegobezie-archives.com/biography/ («He was one of the founders of Me'isone in 1968»)። ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 32። ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 32። ↩
- «Biography», Negede Gobezie Archives, https://www.negedegobezie-archives.com/biography/ («Born on October 15, 1943, in the town of Dessie»). ይህ የነገደ ጎበዜ የራሳቸው ማኅደር ድረ ገጽ ነው። በዚህ ክፍል የተጠቀሱት የሕይወት ታሪክ ዝርዝሮች በሙሉ ከዚሁ ምንጭ የተወሰዱ ናቸው። ↩
- Negede Gobezie, «Parlement et sociétés traditionnelles en Afrique noire: une étude comparative de l'empire d'Éthiopie et de la République de Tanzanie» (thèse de doctorat en droit, Université d'Aix-Marseille III, 1974). ↩
- «Biography», Negede Gobezie Archives («From August 1970 to August 1971 he was president of the ESUE»). ↩
- ባሕሩ ዘውዴ፣ «የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ አሻራ በብሔረሰብ ጥያቄ ላይ» (አንዳርጋቸው ዘመኑን «2013» ብለው ይጠቅሳሉ)፣ አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 40 ላይ እንደተጠቀሰው። ↩
- Walleligne Mekonnen, «On the Question of Nationalities in Ethiopia», Struggle 5:2 (17 November 1969), pp. 2, 4: «In short to be an Ethiopian, you will have to wear an Amhara mask (to use Fanon's expression)»; «There is nothing wrong with secessionism as such.» https://www.marxists.org/history/erol/ethiopia/nationalities.pdf. ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 42። ↩
- Bahru Zewde, «Introduction», in Bahru Zewde, ed., Documenting the Ethiopian Student Movement: An Exercise in Oral History (Addis Ababa: Forum for Social Studies, 2010), p. 16: «The upshot of the Berlin Congress was the adoption of the formula that has been the distinctive mark of the Ethiopian Left over decades and that finally got enshrined in the 1994 Ethiopian Constitution: "the right of nations to self-determination up to and including secession".» ትርጉሙ የጸሐፊው ነው። ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 42፤ Bahru Zewde, «Introduction», p. 16 («largely confined to the two protagonists of the opposing camps, Andreas Eshete and Berhane Meskel Redda»)። ↩
- Bahru Zewde, ed., Documenting the Ethiopian Student Movement, p. 105 (Andreas Eshete: «not one single item of importance was brought up by the leaders of ESUE at that meeting») and p. 114 (Tedla Seyum: «with the possible exception of Negede, the ESUE veterans were not accustomed to speaking in public, but their lack of experience did not mean they did not participate»). ↩
- Programme of the All Ethiopian Socialist Movement (1975), Part III, section D, «Rights and freedoms of nationalities», art. 1: «The right of all nationalities to self-determination up to and including secession is to be recognized. The unity of the nationalities in Ethiopia shall be based on their voluntary will to live together in equality, fraternity, and mutual respect, and on the benefits accruing from mutual assistance». https://www.marxists.org/history/erol/ethiopia/meison-program-eng.pdf. ትርጉሙ የጸሐፊው ነው። ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 40። ↩
- Programme of the All Ethiopian Socialist Movement (1975), Part III, section E, art. 1: «Ethiopia's national independence, sovereignty, integrity and honour shall be staunchly defended …». ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 40–41። ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 33–34። ↩
- አጼ ፋሲለደስ ኢየሱሳውያንን በ1624–25 ዓ.ም. ገደማ (1632–33 እ.አ.አ.) አስወጥተዋል፤ የጃፓን የመዝጊያ አዋጆች በ1625–32 ዓ.ም. ገደማ (1633–39 እ.አ.አ.) ወጥተዋል። ጃፓን በሐምሌ 1845 ዓ.ም. (1853 እ.አ.አ.) በኮሞዶር ፔሪ መርከቦች መምጣት፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በየካቲት 1847 ዓ.ም. (1855 እ.አ.አ.) በአጼ ቴዎድሮስ ንግሥና ከምዕራቡ ዓለም ጋር ግንኙነታቸውን አድሰዋል። ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 43። ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 44። ↩
- John Young, «Bolshevism and National Federalism in Ethiopia», in John Markakis, Günther Schlee and John Young, The Nation State: A Wrong Model for the Horn of Africa (Berlin: Max-Planck-Gesellschaft, 2021), ch. 3: «According to one TPLF veteran, Stalin's (1913) article became a "bible"»; «The constitution's definition of the nation closely followed Stalin.» የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39(5)ን ይመለከቷል። ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 43። ↩
- ነገደ ጎበዜ፣ «ስለ ኢህአዴግ ህገ መንግሥት ስታሊናዊነትና አደገኛነት» (ያልታተመ የታይፕ ጽሑፍ፤ ማኅደሩ 06/02/1995 ብሎ መዝግቦታል)፣ ገጽ 1፣ Negede Gobezie Archives, https://www.negedegobezie.com/wp-content/uploads/2025/05/1.-Constitution-n°-1-06-02-1995.pdf. በጽሑፉ «ስታሊናዊ» የሚለው ቃል በዋነኛነት የሚያመለክተው ሕገ መንግሥቱ የሥልጣን ክፍፍልን አለመቀበሉንና የአንድ ፓርቲ የበላይነትን ማስፈኑን ነው። ↩
- ነገደ ጎበዜ፣ ይድረስ ለግንቦት ከየካቲት (2014 እ.አ.አ.)፣ «የዶ/ር ነገደ ጎበዜ አዲስ መጽሐፍ»፣ ጎልጉል፣ ገጽ 2 ላይ እንደተጠቀሰው (ዳሰሳው የመጽሐፉን ርዕስ «ይድረስ ከየካቲት ለግንቦት» ብሎ ይጠቅሰዋል)፣ https://www.goolgule.com/wp-content/uploads/2014/08/Negede_Zethiopia1.pdf. ↩
- J. V. Stalin, Marxism and the National Question (1913), ch. 2: «The right of self-determination means that a nation may arrange its life in the way it wishes. … It has the right to complete secession.» https://www.marxists.org/reference/archive/stalin/works/1913/03a.htm. V. I. Lenin, The Right of Nations to Self-Determination (1914), ch. 1: «the self-determination of nations means the political separation of these nations from alien national bodies, and the formation of an independent national state». Constitution of the U.S.S.R. (1936), art. 17: «To every Union Republic is reserved the right freely to secede from the U.S.S.R.» ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 41። ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 42። ↩
- ቃለ ምልልሱ በመኢሶን የእንግሊዝኛ ልሳን ላይ «An interview of a militant of ME'ISONE» በሚል ታትሟል፡- New Ethiopia (October 1977), https://www.marxists.org/history/erol/ethiopia/ne-oct-77.pdf. ቃለ ምልልሱን የሰጡት ነገደ ጎበዜ መሆናቸውን፡- Fred Halliday and Maxine Molyneux, The Ethiopian Revolution (London: Verso, 1981), p. 133, n. («the interview given by Negede Gobeze to Le Monde, September 17, 1977»)፤ የራሳቸው ማኅደርም ሰነዱን «Interview de Negede au journal Le Monde» በሚል ርዕስ ይዞታል። ↩
- New Ethiopia (October 1977), pp. 14–15: «Which doesn't mean that we advocate the secession of Erythrea in the present state of affairs. … Of course, under the former regime, all the reactionary forces were opposed to the secession of Erythrea, whereas we supported that struggle because it helped to weaken Haile-Selassie's regime and consequently made the revolutionary side stronger. Such was the position of progressist forces all over the world. Today, things have changed. Even the ex-Crown Prince supports the Independance of Erythrea. This shows clearly the change in the disposition of forces. The aid provided by the Arab reactionary regimes to the Erythrean fronts reveals that this change has been going on an international scale as well. Under such circumstances, our organization is today opposed to the secession of Erythrea.» ትርጉሙ የጸሐፊው ነው። ↩
- New Ethiopia (October 1977), p. 14: «at the moment, the issue of the revolution is closely bound up with the question of territorial integrity in our country». ↩
- ያዕቆብ ኃይለማርያም (ዶ/ር)፣ አሰብ የማን ናት? (የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ) (አዲስ አበባ፣ 2003 ዓ.ም.)፣ ምዕራፍ 2። ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 3፣ 5። ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 15፡- «ከመኢሶን ኃይሌ ፊዳ፣ ዶ/ር ፍቅሬ መርዕድ፣ ዶ/ር ከድር መሀመድ፣ መስፍን ካሱ እና ዶ/ር ነገደ ጎበዜ»። ↩
- «Biography», Negede Gobezie Archives («December 1975–August 1977: Negede served as a member of The Provisional Office for Mass Organizational Affairs (POMOA) … president of the Information and Political Committee»). ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 11፣ የግርጌ ማስታወሻ 17። ↩
- Halliday and Molyneux, The Ethiopian Revolution, p. 131. ↩
- Halliday and Molyneux, The Ethiopian Revolution, pp. 131–132: «Me'ison also vigorously supported the use of terror against their old foes, the EPRP, and a number of Me'ison leaders … most prominent among them Fikre Merid … were assassinated by the EPRP». ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 29–31። ↩
- New Ethiopia (October 1977), p. 17: «before accusing us as well as the DERG of repression and massacres, it must be realized that Ethiopia is now in a state of civil war. Last but not least, this situation is deliberately given an exaggerated importance in order to deceive international opinion.» Halliday and Molyneux, The Ethiopian Revolution, p. 135: «far from making self-criticism for its enthusiastic role in the red terror, it seeks to justify it». ↩
- «Interview with the BBC» (Patrick Gilkes), New Ethiopia (May 1980), pp. 6–9: «the red terror was not organized against ME'ISONE alone. It was organized against all opposition to the military. It was organized to terrorize the whole Ethiopian people». https://www.marxists.org/history/erol/ethiopia/ne-may-80.pdf. ↩
- Andargachew Tiruneh, «The Ethiopian Revolution (1974 to 1984)», p. 324. ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 12። ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 29–30። ↩
- Andargachew Tiruneh, «The Ethiopian Revolution (1974 to 1984)», p. 326. ↩
- «Biography», Negede Gobezie Archives («When Me'isone broke with the DERGUE, Negede was in Lausanne (Switzerland) … Following instructions from Me'isone leaders he decided not to return to Ethiopia»). ↩
- «Biography», Negede Gobezie Archives («September 1977–April 1978: Invited by the leaders of Cuba and Yemen, he stayed in both of these countries … Negede went to Addis Abeba and stayed for two months there at the Cuban embassy»). ↩
- Die Welt, 24 May 1978, Joseph Hansen, «Castro, Mengistu Differ on Eritrea», Intercontinental Press 16:24 (19 June 1978) ላይ እንደተጠቀሰው፡- «During Mengistu's April 21–27 visit to Havana, Negede Gobeze was smuggled out of Paris into Ethiopia by way of Aden». ያው ጽሑፍ የVictoria Brittainን ዘገባ (Manchester Guardian Weekly, 4 June 1978) ይጠቅሳል፡- «the Cuban attempt to get a dialogue going between the Dergue and the Meison leader … failed completely». ሁለቱ ምንጮች በቆይታው ርዝመት ይለያያሉ፤ ማኅደሩ ሁለት ወር ሲል «ዲ ቬልት» መግባታቸውን በኤፕሪል መጨረሻ ያደርገዋል። https://www.themilitant.com/Intercontinental_Press/1978/IP1624.pdf. ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 33። የጠቀሱት ጽሑፍ፡- Gebru Tareke, «The Red Terror in Ethiopia: A Historical Aberration», Journal of Developing Societies 24 (June 2008), p. 183። ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 33። ↩
- Bahru Zewde, The Quest for Socialist Utopia: The Ethiopian Student Movement, c. 1960–1974 (Woodbridge: James Currey, 2014), pp. 273–278, Samuel Andreas Admasie በ International Review of Social History 59:3 (2014), pp. 534–537 ላይ ባቀረቡት ግምገማ እንደተጠቃለለው፡- «the two major legacies – both deemed entirely negative – of the student movement can be found in the establishment of an intolerant and acrimonious political culture and in the lingering power of the discourse of the national question». ↩
- «Biography», Negede Gobezie Archives («1980 created Comité de Solidarité avec l'Ethiopie»; «1997 Founder and director of Radio Selam»; «1997–2002 founder and Director of Radio Keste Damena»; «Chairman of Union of Ethiopian Opposition Organisations … in 1998»; «A conference on "From War to Peace, and from Dictatorship to Democracy," held in July 1993 in Paris»; «chairman of the Peace and Reconciliation Conference, which was organized in December 1993 in Addis Abeba»; «coordinator of Ethiopian Political Parties Conference in 1998»). ↩
- New Ethiopia (October 1977), p. 16: «Forming an alliance with such forces against the military regime is out of question.» ↩
- ነገደ ጎበዜ፣ ይድረስ ለግንቦት ከየካቲት፣ ጎልጉል፣ ገጽ 2 ላይ እንደተጠቀሰው። ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 32። ↩
- አንዳርጋቸው አሰግድ፣ የ1966 ሕዝባዊ አብዮት እና መኢሶን፣ ገጽ 33። ↩
